18 በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።
19 “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ።
20 ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤
21 ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።
22 “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል።
23 ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን?
24 “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።