1 እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤
2 ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።
3 ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኵሰት ወይም የስስት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና።
4 የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰ ግኑ ሁኑ።
5 ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።
6 ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው።