ኤፌሶን
ምዕራፎች 5
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤
2ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።
3ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኵሰት ወይም የስስት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና።
4የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰ ግኑ ሁኑ።
5ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።
6ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው።
7ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ።
8ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤
9የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና።
10እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ።
11ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤
12በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና።
13ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤
14ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣“አንተ የተኛህ ንቃ፤ከሙታን ተነሣ፤ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል።
15እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ።
16ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።
17ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ።
18በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና።
19በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም።
20በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁል ጊዜ አመስግኑ።
21ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።