1 እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ከሰዎች መካከል ይመረጣል፤ የእግዚአብሔርም በሆነው ነገር ላይ ሰዎችን በመወከል ለኀጢአት የሚሆነውን መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል።
2 እርሱ ራሱ ድካም ያለበት በመሆኑ፣ አላዋቂ ለሆኑትና ለሚባዝኑት ሊራራላቸው ይችላል።
3 ስለ ራሱ ኀጢአትና ስለ ሌሎች ሰዎች ኀጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የተገባው በዚሁ ምክንያት ነው።
4 አሮን እንደ ተጠራ በእግዚአብሔር መጠራት አለበት እንጂ፣ ይህን ክብር ለራሱ የሚወስድ ማንም የለም።
5 እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፣“አንተ ልጄ ነህ፤እኔ ዛሬ አባት ሆንሁህ” አለው።
6 እንዲሁም በሌላ ስፍራ፣“እንደ መልከጼዴቅ ሹመት፣አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል።