6 የካህናት አለቆችና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው።
7 አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።
8 ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤
9 ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።
10 ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው።
11 ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው።
12 ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ።