8 ከዚህም በላይ ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን አጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ፤
9 ሕግ በመጠበቅ የሚገኝ የራሴ ጽድቅ ኖሮኝ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣ ከእምነትም በሆነ ጽድቅ በእርሱ ዘንድ እንድገኝ ነው።
10 ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ፤
11 ለሙታን ትንሣኤም እንድደርስ እናፍቃለሁ።
12 ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ።
13 ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ።
14 እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።