2 ሰንባላጥና ጌሳም፣ “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንገናኝ” ሲሉ ይህችን መልእክት ላኩብኝ። እነርሱ ግን እኔን ለመጒዳት ዐቅደው ነበር።
3 እኔም፣ “ታላቅ ሥራ እየሠራሁ ስለ ሆነ፣ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት ይህን መልስ የሚያደርሱ መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላክሁ።
4 አራት ጊዜም ይህንኑ ዐይነት መልእክት ላኩብኝ፤ እኔም በእያንዳንዱ ጊዜ ያንኑ መልስ ሰጠሁ።
5 ከዚያም ሰንባላጥ ለአምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤
6 የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤“አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደ ምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቶአል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጦአል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣
7 ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።”
8 እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት።