18 የእግዚአብሔርን ቀን ለምትሹ፣ለእናንተ ወዮላችሁ የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትሻላችሁ?ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።
19 ይህ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሲሸሽ፣ድብ እንደሚያጋጥመው፣ወደ ቤቱም ገብቶ፣ እጁን በግድግዳውላይ ሲያሳርፍ፣እባብ እንደሚነድፈው ነው።
20 የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ፣የብርሃን ጸዳል የሌለው ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?
21 “ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤ጠልቼውማለሁ፤ ጉባኤዎቻችሁ ደስ አያሰኙኝም።
22 የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ብታቀርቡልኝም፣እኔ አልቀበለውም፤ከሰቡ እንስሶቻችሁ የኅብረት መሥዋዕት ብታቀርቡልኝም፣እኔ አልመለከተውም።
23 የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤የበገናህንም ዜማ አልሰማም።
24 ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።