1 እኔም፣ ሜዶናዊው ዳርዮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ እርሱን ለማገዝና ለማበረታታት በአጠገቡ ቆሜ ነበር።
2 “አሁንም እውነቱን እነግርሃለሁ፤ እነሆ፣ ሦስት ሌሎች ነገሥታት በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል። በባለጠግነቱም እጅግ በበረታ ጊዜ፣ ሌላውን ሁሉ አሳድሞ በግሪክ መንግሥት ላይ ያስነሣል።
3 ከዚያም በታላቅ ኀይል የሚገዛና የወደደውንም ሁሉ የሚያደርግ ኀያል ንጉሥ ይነሣል።
4 በኀይል እየገነነ ሳለም፣ መንግሥቱ ይፈርሳል፤ ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳትም ይከፋፈላል። መንግሥቱ ተወስዶ ለሌሎች ስለሚሰጥ፣ ለዘሩ አይተላለፍም፤ ኀይሉም እንደ መጀመሪያው አይሆንም።
5 “የደቡቡ ንጉሥ ይበረታል፤ ነገር ግን ከጦር አዛዦቹ አንዱ ከእርሱ የበለጠ የበረታ ይሆናል፤ ግዛቱም ታላቅ ይሆናል።
6 ከጥቂት ዓመታት በኋላም አንድነት ይፈጥራሉ። የደቡቡ ንጉሥ ሴት ልጅ ስምምነት ለማድረግ ወደ ሰሜኑ ንጉሥ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ኀይሏን ይዛ መቈየት አትችልም፤ እርሱም ሆነ የእርሱ ኀይል አይጸናም። በእነዚያ ቀናት እርሷ ከቤተ መንግሥት አጃቢዎቿ፣ ከአባቷና ከደጋፊዎቿ ጋር ዐልፋ ትሰጣለች።
7 “ከዘመዶቿ አንዱ ስፍራዋን ሊይዝ ይነሣል፤ የሰሜንን ንጉሥ ሰራዊት ይወጋል፤ ምሽጎቹንም ጥሶ ይገባል፤ ከእነርሱም ጋር ተዋግቶ ድል ያደርጋል።
8 አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብፅም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ከመዋጋት ይቈጠባል።
9 የሰሜኑም ንጉሥ፣ የደቡቡን ንጉሥ ግዛት ይወራል፤ ነገር ግን አፈግፍጎ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።
10 ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እስከ ጠላት ምሽግ ደርሶ የሚዋጋና ሊቋቋሙት እንደማይቻል ጐርፍ የሚጠራርግ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባሉ።
11 “ከዚያም የደቡቡ ንጉሥ በቊጣ ወጥቶ የሰሜኑን ንጉሥ ይወጋል። የሰሜኑ ንጉሥ ታላቅ ሰራዊት ቢያሰባስብም ይሸነፋል።
12 የደቡቡ ንጉሥ ብዙ ሰራዊት በሚማርክበት ጊዜ ልቡ በትዕቢት ይሞላል፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችንም ይገድላል፤ ነገር ግን በድል አድራጊነቱ አይጸናም።
13 የሰሜን ንጉሥ ከመጀመሪያው የሚበልጥ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባል፤ ከብዙ ዓመትም በኋላ በትጥቅ እጅግ ከተደራጀ ታላቅ ሰራዊት ጋር ተመልሶ ይመጣል።
14 “በዚያም ዘመን ብዙዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ራእዩ ይፈጸም ዘንድ፣ ከሕዝብህ መካከል ዐመፀኛ የሆኑ ሰዎች ይነሣሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም።
15 የሰሜኑም ንጉሥ መጥቶ የዐፈር ድልድል ይክባል፤ የተመሸገችውንም ከተማ ይይዛል። የደቡቡ ሰራዊትም ለመቋቋም ኀይል ያጣል፤ የተመረጡት ተዋጊዎቻቸው እንኳ ጸንተው መዋጋት አይችሉም።
16 ወራሪው ደስ ያሰኘውን ያደርጋል፤ ማንም ሊቋቋመው አይችልም። በመልካሚቱ ምድር ላይ ይገዛል፤ እርሷን ለማጥፋትም ኀይል ይኖረዋል።
17 በመንግሥቱ ያለውን ሰራዊት ሁሉ ይዞ ለመምጣት ይወስናል፤ ከደቡብም ንጉሥ ጋር ይስማማል፤ ይህንም መንግሥት ለመጣል ሴት ልጁን ይድርለታል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ አይሳካለትም፤ ያሰበውም ነገር አይጠቅመውም።
18 ከዚህም በኋላ በባሕር ጠረፍ ወዳሉት አገሮች ፊቱን በመመለስ ብዙዎቹን ይይዛል፤ ነገር ግን አንድ አዛዥ ትዕቢቱን ያከሽፍበታል፤ በራሱም ላይ ይመልስበታል።
19 በገዛ አገሩ ወዳሉት ምሽጎችም ፊቱን ይመልሳል፤ ነገር ግን ተሰናክሎ ይወድቃል፤ ዳግምም አይታይም።
20 “በእርሱ ቦታ የሚተካውም የመንግሥቱን ክብር ለማስጠበቅ ግብር አስገባሪ ይልካል፤ ይሁን እንጂ በቊጣ ወይም በጦርነት ሳይሆን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይገደላል።
21 “በእርሱም ፋንታ የተናቀ ሰው ይነግሣል፤ ንጉሣዊ ክብርም አይሰጠውም፤ ሕዝቡ በሰላም ተቀምጦ ሳለ በተንኰል መንግሥቱን ይይዛል።
22 ከፊቱ የሚቆመውን ታላቅ ሰራዊት፣ የቃል ኪዳኑንም አለቃ ሳይቀር ይደመስሳል።
23 ከእርሱ ጋር ስምምነት ከተደረገ በኋላ የማታለል ሥራውን ይሠራል፤ ከጥቂት ሰዎች ጋር ለሥልጣን ይበቃል።
24 የበለጸጉትን ክፍለ አገሮች በሰላም ሳሉ በድንገት ይወርራቸዋል፤ አባቶቹም ሆኑ አያቶቹ ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል፤ ይከናወንለታልም፤ ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና የተገኘውን ሀብት ሁሉ ለተከታዮቹ ያካፍላቸዋል፤ ምሽጎችን ለመጣል ያሤራል፤ ይህን የሚያደርገውም ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።
25 “ታላቅ ሰራዊት አደራጅቶ ኀይሉንና ብርታቱን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያነሣሣል፤ የደቡብ ንጉሥም ቊጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኀያል ሰራዊት ይዞ ጦርነትን ያውጃል፤ ነገር ግን ከተዶለተበት ሤራ የተነሣ መቋቋም አይችልም።
26 ከንጉሥ ማዕድ አብረውት ሲበሉ የነበሩት ሊያጠፉት ያሤራሉ፤ ሰራዊቱም ይደመሰሳል፤ ብዙዎቹም በጦርነት ይወድቃሉ።
27 ልባቸው ወደ ክፋት ያዘነበለው ሁለቱ ነገሥታት፣ በአንድ ገበታ አብረው ይቀመጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ሐሰትን ይነጋገራሉ፤ ነገር ግን የተወሰነው ጊዜ ገና ስለ ሆነ አይከናወንላቸውም።
28 የሰሜን ንጉሥ ብዙ ሀብት ይዞ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል፤ ነገር ግን ልቡ በተቀደሰው ኪዳን ላይ ይነሣሣል፤ ክፉ ነገርም ያደርግበታል፤ ከዚያም ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።
29 “በተወሰነው ጊዜ ደቡቡን እንደ ገና ይወራል፤ በዚህ ጊዜ ግን ውጤቱ ከበፊቱ የተለየ ይሆናል።
30 የኪቲም መርከቦች ይቃወሙታል፤ ልቡም ይሸበራል። ወደ ኋላም ይመለሳል፤ ቊጣውን በተቀደሰው ኪዳን ላይ ያወርዳል፤ ተመልሶም የተቀደሰውን ኪዳን የተውትን ይንከባከባል።
31 “የጦር ሰራዊቶቹም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሩን ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ በዚያም ጥፋትን የሚያመጣውን የጥፋት ርኵሰት ይተክላሉ፤
32 ኪዳኑን የሚተላለፉትን በማታለል ያስታል፤ አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ጸንተው ይቃወሙታል፤ እርምጃም ይወስዳሉ።
33 “ለጊዜው በሰይፍ ቢወድቁም፣ ቢቃጠሉም፣ ቢማረኩና ቢዘረፉም፣ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ብዙዎችን ያስተምራሉ።
34 በሚወድቁበት ጊዜ መጠነኛ ርዳታ ያገኛሉ፤ እውነተኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎችም ይተባበሯቸዋል።
35 ጥበበኛ ከሆኑ ሰዎች አንዳንዶቹ ይሰናከላሉ፤ ይህም እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የጠሩ፣ የነጠሩና እንከን የሌለባቸው ይሆኑ ዘንድ ነው፤ የተወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰምና።
36 “ንጉሡ ደስ እንዳለው ያደርጋል፤ ከአማልክት ሁሉ በላይ ራሱን እጅግ ከፍ በማድረግ በአማልክት አምላክ ላይ ተሰምቶ የማይታወቅ የስድብ ቃል ይናገራል፤ የቊጣውም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ይሳካለታል፤ የተወሰነው ነገር ሁሉ መሆን አለበትና።
37 ሴቶች ለሚወዱትም ሆነ ለአባቶቹ አማልክት ክብርን አይሰጥም፤ ማንኛውንም አምላክ አያከብርም፤ ነገር ግን ራሱን ከእነዚህ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል።
38 በእነርሱም ምትክ የምሽጎችን አምላክ ያከብራል፤ አባቶች የማያውቁትን አምላክ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮችና በውድ ስጦታዎች ያከብራል።
39 በባዕድ አምላክ ርዳታ ጽኑ ምሽጎችን ይወጋል፤ ለእርሱ የሚገዙትን በእጅጉ ያከብራቸዋል፤ በብዙ ሕዝብ ላይ ገዦች ያደርጋቸዋል፤ ምድሩንም በዋጋ ያከፋፍላቸዋል።
40 “በመጨረሻው ዘመን የደቡብ ንጉሥ ጦርነት ያውጅበታል፤ የሰሜን ንጉሥም በፈረሰኞችና በሠረገሎች፣ በብዙ መርከቦችም እንደ ማዕበል ይመጣበታል፤ ብዙ አገሮችን ይወራል፤ እንደ ጐርፍም እየጠራረገ በመካከላቸው ያልፋል።
41 መልካሚቱንም ምድር ይወራል፤ ብዙ አገሮች በእጁ ይወድቃሉ፤ ኤዶም፣ ሞዓብና የአሞን መሪዎች ግን ከእጁ ያመልጣሉ።
42 ሥልጣኑን በብዙ አገሮች ላይ ያንሰራፋል፤ ግብፅም አታመልጥም።
43 የወርቅና የብር ክምችትን፣ እንዲሁም የግብፅን ሀብት ሁሉ በቊጥጥሩ ሥር ያደርጋል፤ የሊቢያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይገዙለታል።
44 ነገር ግን ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣ ወሬ ያስደነግጠዋል፤ ብዙዎችንም ለማጥፋትና ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል።
45 ንጉሣዊ ድንኳኖቹን በባሕሮች መካከል ውብ በሆነው ቅዱስ ተራራ ላይ ይተክላል፤ ይሁን እንጂ ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ ማንም አይረዳውም።