ዳንኤል 8 NASV

ዳንኤል በራእዩ ያየው አውራ በግና ፍየል

1 ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ አስቀድሞ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ እኔ ዳንኤል ሌላ ራእይ አየሁ።

2 በራእዩም፣ በኤላም አውራጃ በሱሳ ግንብ ራሴን አየሁት፤ በራእዩም በኡባል ወንዝ አጠገብ ነበርሁ፤

3 ዐይኔን አንሥቼ ስመለከት እነሆ፤ ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ በወንዙ አጠገብ ቆሞ አየሁ፤ ቀንዶቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ ከቀንዶቹም አንዱ ከሌላው ይረዝማል፤ የበቀለው ግን ዘግይቶ ነበር።

4 አውራ በጉም ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ። ምንም ዐይነት እንስሳ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም ሊያድን የሚችል አልነበረም፤ የፈለገውን ሁሉ አደረገ፤ ታላቅም ሆነ።

5 ስለዚህም ነገር እያሰብሁ ሳለሁ፣ በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል፣ መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ፤

6 በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት፣ ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርድሮ መጣበት፤ በታላቅ ቊጣም መታው፤

7 እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጐዳ አየሁ፤ አውራ በጉም ለመቋቋም ጒልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራ በጉንም ከፍየሉ እጅ ለማዳን የሚችል አልነበረም።

8 ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኀይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ።

9 ከእነዚህም ቀንዶች መካከል በአንዱ ላይ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ መልካሚቱ ምድር በኀይል አደገ።

10 ወደ ሰማይ ሰራዊት እስኪደርስ ድረስ አደገ፤ ከከዋክብት ሰራዊትም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም።

11 ከሰማይ ሰራዊት አለቃ ጋር እስኪተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የልዑሉንም የዘወትር መሥዋዕት ወሰደበት፤ የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ።

12 ከዐመፅ የተነሣም የቅዱሳን ሰራዊት ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለእርሱ አልፎ ተሰጠ፤ የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት፤ እውነትም ወደ ምድር ተጣለች።

13 ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እንዲህ አለው፤ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ ለጥፋት ምክንያት ስለ ሆነው ዐመፅ፣ ከእግር በታች እንዲረገጡ አልፈው ስለሚሰጡት መቅደስና ሰራዊት የታየው ራእይ የሚፈጸመው መቼ ነው?”

14 እርሱም፣ “እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ምሽቶችና ማለዳዎች ድረስ ይቈያል፤ ከዚያም መቅደሱ እንደ ገና ይነጻል” አለኝ።

የራእዩ ትርጓሜ

15 እኔ ዳንኤል ራእዩን ስመለከትና ሳስተውል ሳለ፣ ሰውን የሚመስል ከፊት ለፊቴ ቆመ፤

16 ከኡባልም፣ “ገብርኤል ሆይ፤ ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጒም ንገረው” ብሎ የሚጮኽ የሰው ድምፅ ሰማሁ።

17 እኔ ወደ ቆምሁበት ስፍራ እየቀረበ ሲመጣ፣ ደንግጬ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ራእዩ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እንደሆነ አስተውል” አለኝ።

18 እየተናገረኝ ሳለ፣ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ በከባድ እንቅልፍም ተዋጥሁ፤ እርሱ ግን ዳሰሰኝና በእግሮቼ አቆመኝ።

19 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ራእዩ በመጨረሻው ዘመን ሊሆን ያለውን የሚያመለክት ስለ ሆነ፣ በኋላ በቊጣው ዘመን ምን እንደሚሆን እነግርሃለሁ፤

20 ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል።

21 ጠጒራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው።

22 የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶች፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታት ያመለክታሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም።

23 “በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል።

24 እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኀይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኀያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል።

25 እያጭበረበረ ይበለጽጋል፤ ራሱንም ታላቅ አድርጎ ይቈጥራል። በሰላም ተደላድለን ተቀምጠናል ሲሉ፣ ብዙዎችን ያጠፋል፤ በልዑላን ልዑልም ላይ ይነሣል፤ ይሁን እንጂ እርሱም ይጠፋል፤ ነገር ግን በሰው ኀይል አይደለም።

26 “የተሰጠህ የምሽቱና የማለዳው ራእይ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ የሚሆነውን ስለሚያመለክት ራእዩን ዝጋው።”

27 እኔ ዳንኤል ዐቅሜ ተሟጦ ነበር፤ ለብዙ ቀናት ታመምሁ፤ ተኛሁም። ከዚያም በኋላ ተነሥቼ ወደ ንጉሡ ሥራ ሄድሁ። ባየሁት ራእይ ተደናግጬ ነበር፤ ነገሩም አልገባኝም።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12