13 ስለዚህ ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎቹ ከቅዒላ ተነሥተው መሄድ ወደሚችሉበት ቦታ ሁሉ ሄዱ፤ ዳዊት ከቅዒላ መሸሹን በሰማ ጊዜ፣ ሳኦል ወደዚያ መሄዱን ተወ።
14 ዳዊት በምድረ በዳ ባሉ ምሽጎችና በዚፍ ምድረ በዳ ኰረብታዎች ተቀመጠ፤ ሳኦልም በየዕለቱ ይከታተለው ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳዊትን አሳልፎ አልሰጠውም።
15 ዳዊት በዚፍ ምድረ በዳ ሖሬሽ በተባለ ቦታ ሳለ፣ ሳኦል ሊገድለው መምጣቱን አየ።
16 የሳኦል ልጅ ዮናታንም ዳዊት ወዳለበት ወደ ሖሬሽ ሄዶ፣ በእግዚአብሔር ስም አበረታታው፤
17 እርሱም፣ “አትፍራ፤ አባቴ ሳኦል እጁን በአንተ ላይ አያሳርፍም፤ በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ፤ ይህንም አባቴ ሳኦል እንኳ ያውቀዋል” አለው።
18 ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ። ከዚያም ዮናታን ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊት ግን እዚያው ሖሬሽ ተቀመጠ።
19 የዚፍ ሰዎች ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል ወጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ ዳዊት ከየሴሞን በስተ ደቡብ በኤኬላ ኰረብታ ላይ በሖሬሽ ምሽጎች ውስጥ በመካከላችን ተደብቆ የለምን?