23 ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
24 እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው።
25 እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር።
26 ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ።
27 የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ።
28 ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኛ ሁላችን እዚሁ ስላለን፣ በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርስ!” ብሎ ጮኸ።
29 የወህኒ ቤቱ ጠባቂም መብራት ለምኖ ወደ ውስጥ ዘሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ላይ ወደቀ፤