7 ብዙ ቀን በዝግታ እየተጓዝን ቀኒዶስ አካባቢ በጭንቅ ደረስን፤ ነፋሱም ወደ ፊት እንዳንሄድ በከለከለን ጊዜ፣ በሰልሙና አጠገብ አድርገን በቀርጤስ ተተግነን ሄድን፤
8 ጥግ ጥጉንም ይዘን፣ በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው፣ ‘መልካም ወደብ’ ወደተባለ ስፍራ በጭንቅ ደረስን።
9 ብዙ ጊዜ ባክኖ፤ የጾሙ ጊዜ ስላለፈ በመርከብ መጓዙ አደገኛ ሆኖ ነበርና ጳውሎስ፣
10 “እናንት ሰዎች፤ ጒዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጒዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው።
11 የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር።
12 ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጒዞአችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር።
13 መጠነኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው መልሕቁን ነቅለው፣ የቀርጤስን ዳርቻ በመያዝ ተጓዙ።