1 ተሰሎንቄ 2 NASV

የጳውሎስ አገልግሎት በተሰሎንቄ

1 ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ የመጣነው ለከንቱ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

2 እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደር ስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን።

3 የምናቀርበው ልመና ከስሕተት ወይም ከክፉ ዐላማ ወይም እናንተን ለማታለል ከመፈለግ የመነጨ አይደለም።

4 ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ብለን አይደለም።

5 የሽንገላ ቃል ከቶ እንዳልተናገርን ወይም ሥሥትን ለመሸፈን ብለን አስመሳዮች እንዳልሆንን ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው።

6 ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንባችሁ ነበር፤

7 ነገር ግን እናት ልጅዋን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን።

8 የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ።

9 ወንድሞች ሆይ፤ ጥረታችንንና ድካማችንን ታስታውሳላችሁ፤ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እየሠራን ወንጌል ሰበክንላችሁ።

10 በእናንተ በምታምኑት መካከል ሳለን እንዴት በቅድስና፣ በጽድቅ እንዲሁም ያለ ነቀፋ ሆነን እንደኖርን እናንተም እግዚአብሔርም ምስክሮች ናችሁ።

11 አባት ለገዛ ልጆቹ እንደሚሆን እኛም ለእያንዳንዳችሁ የቱን ያህል እንደሆንን ታውቃላችሁና፤

12 ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትኖሩ ዘንድ አበረታታናችሁ፤ አጽናናችሁ፤ አጥብቀንም ለመንናችሁ።

13 ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእናንተ በምታምኑት ዘንድ በርግጥ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ እናመሰግናለን።

14 ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን በይሁዳ የሚገኙትን የእግዚአብሔርን አብያተ ክርስቲያናት መስላችኋል፤ እነዚያ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፣ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራን ተቀብላችኋል።

15 እነርሱ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም አሳደዱን፤ እግዚአብሔርንም ደስ አላሰኙትም፤ የሰውም ሁሉ ፀር ሆኑ፤

16 ይኸውም ይድኑ ዘንድ ለአሕዛብ እንዳንናገር ለመከልከል ነው፤ በዚህ ሁኔታ ኀጢአታቸውን ሁል ጊዜ በራሳቸው ላይ እስከ መጨረሻው እያከማቹ ይሄዳሉ። ቊጣውም በእነርሱ ላይ ያለ ልክ መጥቶአል።

ጳውሎስ የተሰሎንቄን ሰዎች ለማየት የነበረው ናፍቆት

17 ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ እኛ በልባችን ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ብንለይም፣ ለእናንተ ካለን ታላቅ ናፍቆት የተነሣ ፊታችሁን ለማየት ብርቱ ጥረት አደረግን።

18 ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን አዘገየኝ።

19 ጌታችን ኢየሱስ ሲመጣ በእርሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም አክሊላችን ማን ነው? እናንተ አይደላችሁምን?

20 በርግጥ ክብራችንም ደስታችንም ናችሁ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5