1 ሳሙኤል 13:10-16 NASV

10 ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም ሊቀበለው ወጣ።

11 ሳሙኤልም፣ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ሰራዊቱ መበታተኑን፣ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፣ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤

12 ‘ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም’ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።”

13 ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤

14 አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠ በቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።”

15 ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።

16 ፍልስጥኤማውያን በማክማስ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ ሳኦል፣ ልጁ ዮናታንና አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ነበሩ።