1 ሳሙኤል 15:10-16 NASV

10 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፤

11 “ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ፤ እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፣ ትእዛዜንም አልፈጸመምና።” ሳሙኤልም እጅግ ተጨንቆ፣ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

12 ሳሙኤልም ጠዋት ተነሥቶ በማለዳ ሳኦልን ለመገናኘት ሄደ፤ ነገር ግን፣ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዶአል፤ ለራሱ ክብር የመታሰቢያ ሐውልት በዚያ ካቆመ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወርዶአል” ተብሎ ተነገረው።

13 ሳሙኤል ባገኘው ጊዜ ሳኦል፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው።

14 ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

15 ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።

16 ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “ስማ! ትናንት ማታ እግዚአብሔር የነገረኝን ልንገርህ?” አለው።ሳኦልም፣ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት።