1 ሳሙኤል 16:1-6 NASV

1 እግዚአብሔር ሳሙኤልን፣ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ” አለው።

2 ሳሙኤል ግን፣ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፣ ‘ለእግዚአብሔር ልሠዋ መጥቻለሁ’ በል።

3 እሴይን ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።”

4 ሳሙኤል እግዚአብሔር ያለውን ነገር አደረገ። ቤተ ልሔም እንደ ደረሰም፣ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፣ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት።

5 ሳሙኤልም፣ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው።

6 እዚያ በደረሱ ጊዜም፣ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞአል” ብሎ አሰበ።