21 ሳኦልም በልቡ፣ “ወጥመድ እንድትሆነው፣ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን፣ “እነሆ፤ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው።
22 ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፣ “ለዳዊት፣ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለ ሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው።
23 እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ አማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቈጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እምብዛም የማልታወቅ ሰው ነኝ” አላቸው።
24 የሳኦል ባለሟሎችም ዳዊት ያላቸውን በነገሩት ጊዜ፣
25 ሳኦል፣ “ዳዊትን፣ ‘ንጉሡስ ለልጅቱ ካንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን ለመበቀል የመቶ ፍልስጥኤማውያንን ሸለፈት እንጂ ሌላ አይደለም ብላችሁ ንገሩት’ ” አላቸው። ሳኦል ይህን ያቀደው ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ነበር።
26 ባለሟሎቹ ይህን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሥ ዐማች መሆኑ ደስ አሰኘው። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት፣
27 ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎቹ ሄደው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ለንጉሡ ዐማች ይሆን ዘንድ፣ ሸለፈታቸውን አምጥቶ በቊጥራቸው ልክ ለንጉሡ አቀረበ፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት።