2 ዮናታንም፣ “ይህስ ከቶ አይሁንብህ፤ አትሞትም! እነሆ፤ አባቴ ትልቅም ይሁን ትንሽ ማናቸውንም ነገር አስቀድሞ ሳይነግረኝ አያደርገውም። ታዲያ አባቴ ይህን ለምን ይደብቀኛል? ነገሩ እንዲህ አይደለም” ብሎ መለሰለት።
3 ዳዊት ግን፣ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሎአል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በነፍስህ እምላለሁ በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀርቶአል” ብሎ ማለ።
4 ዮናታንም ዳዊትን፣ “እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው።
5 ስለዚህ ዳዊት እንዲህ አለ፤ ‘እነሆ፤ ነገ የወር መባቻ በዓል ስለ ሆነ፣ ከንጉሡ ጋር ምሳ መብላት ይጠበቅብኛል፤ ነገር ግን እስከ ከነገ ወዲያ ማታ ድረስ ከዱር ልደበቅ፤
6 አባትህ ከፈለገኝ፣ ‘ለቤተ ዘመዶቹ ሁሉ ዓመታዊ መሥዋዕት የሚቀርብ ስለ ሆነ፣ ዳዊት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ቤተ ልሔም ቶሎ ለመሄድ አጥብቆ ፈቃድ ጠየቀኝ’ ብለህ ንገረው።
7 እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፣ አገልጋይህን የሚያሰጋው የለም፤ ከተቈጣ ግን፣ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግ ጣለህ።
8 አንተ ግን፤ ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ፣ ከአገልጋይህ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና። እኔ በደለኛ ከሆንሁ፣ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!”