1 ሳሙኤል 26:4-10 NASV

4 ሰላዮች ልኮ በትክክል ሳኦል መምጣቱን አረጋገጠ።

5 ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሰራዊቱ አለቃ፣ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ። ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ሳለ፣ ሰራዊቱ በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።

6 ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፣ “ወደ ሳኦል ሰፈር አብሮኝ የሚወርድ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው።አቢሳም፣ “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።

7 ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሰራዊቱ ወዳለበት ሄዱ። እነሆ፤ ሳኦል በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ጦሩም ራስጌው አጠገብ በመሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተው ነበር።

8 አቢሳም ዳዊትን፣ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው።

9 ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው?

10 ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል።