1 ሳሙኤል 26:8-14 NASV

8 አቢሳም ዳዊትን፣ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው።

9 ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው?

10 ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል።

11 እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”

12 ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውሃውን መያዣ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ፤ ይህን ያየም ሆነ ያወቀ ወይም የነቃ ማንም አልነበረም። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለወደቀባቸው ሁሉም ተኝተው ነበርና።

13 ከዚህ በኋላ ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በኰረብታው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበር።

14 ዳዊት ሰራዊቱንና የኔርን ልጅ አብኔርን፣ “አበኔር ሆይ፣ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ።አበኔርም፣ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ።