8 በዚያ ጊዜም ዳዊትና ሰዎቹ ወጥተው ጌሹራውያንን፣ ጌርዛውያንንና አማሌቃውያንን ወረሩ። እነዚህ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ፣ እስከ ሱርና እስከ ግብፅ ባለው ምድር ላይ ይኖሩ ነበር።
9 ዳዊትም ምድሪቱን በመታበት ጊዜ፣ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አላስቀረም፤ ነገር ግን በጎችንና ላሞችን፣ አህዮችንና ግመሎችን እንዲሁም ልብሶችን ወሰደ፤ ወደ አንኩስም ተመለሰ።
10 አንኩስም፣ “ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ?” ሲል በጠየቀው ጊዜ ዳዊት፣ “የዘመትነው በይሁዳ ደቡብ፣ ወይም በይረሕምኤላውያን ደቡብ፣ ወይም በቄናውያን ደቡብ ላይ ነው” በማለት ይመልስ ነበር።”
11 ዳዊት “ ‘እርሱ እንዲህ አድርጎአል’ ብለው ይነግሩብናል” ብሎ ስላሰበ፣ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አስቀርቶ ወደ ጌት አላመጣም። በፍልስጥኤም ግዛት በኖረበት ዘመን ሁሉ፣ እንዲህ ማድረጉ የተለመደ ነበር።
12 አንኩስም በልቡ፣ “እርሱ ራሱ የገዛ ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን እጅግ እንዲጠሉት ስላደረገ፣ ለዘላለም አገልጋዬ ይሆናል” ብሎ ስላሰበ ዳዊትን አመነው።