1 ሳሙኤል 28:8-14 NASV

8 ስለዚህ ሳኦል ሌላ ልብስ በመልበስ መልኩን ለውጦ ከሁለት ሰዎች ጋር በሌሊት ወደ ሴቲቱ ሄደ። እርሱም፣ “እባክሽ፣ መናፍስትን ጠይቂልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት።

9 ሴትዮዋ ግን፣ “እነሆ፤ ሳኦል ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ እንዴት እንዳጠፋና ያደረገባቸውን ታውቃለህ፤ ታዲያ፣ ታስገድለኝ ዘንድ በሕይወቴ ላይ ወጥመድ የዘረጋኸው ለምንድን ነው?” አለችው።

10 ሳኦልም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም” ሲል በእግዚአብሔር ስም ማለላት።

11 ሴትዮዋም፣ “ማንን ላስነሣልህ?” ብላ ጠየቀችው።እርሱም፣ “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት።

12 ሴትዮዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኽች፤ ሳኦልንም፣ “አንተ ሳኦል ሆነህ ሳለ፣ ለምን አታለልኸኝ?” አለችው።

13 ንጉሡም፣ “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት።ሴትዮዋም፣ “አንድ መንፈስ ከምድር ሲወጣ አያለሁ” አለችው።

14 እርሱም፣ “መልኩ ምን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት።እርሷም፣ “ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየወጣ ነው” አለችው።ሳኦልም ሴትዮዋ ያየችው ሳሙኤል መሆኑን ዐወቀ፤ በመሬትም ላይ ተደፍቶ እጅ ነሣ።