1 ሳሙኤል 5:8-12 NASV

8 ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች በሙሉ ጠርተው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን እናድርገው?” ሲሉ ጠየቁ።እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደ ጌት ውሰዱት” አሏቸው። ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወሰዱት።

9 ነገር ግን ታቦቱን ወደዚያ ከወሰዱት በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በከተማዪቱ ላይ ሆነ፤ ታላቅ መሸበርም አመጣባቸው፤ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል ሕዝቡን በእባጭ መታ።

10 ስለዚህ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ አቃሮን ሰደዱት።የእግዚአብሔር ታቦት እዚያ ሲገባም፣ የአቃሮን ሕዝብ፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ያመጡብን እኛንና ሕዝባችንን ለማስፈጀት ነው” በማለት ጮኹ።

11 የእግዚአብሔር እጅ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ሞት ከተማዪቱን እጅግ አስደንግጦአት ነበርና ሕዝቡ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች በሙሉ ጠርተው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ ወደ ገዛ ስፍራው ይመለስ፤ ያለዚያ እኛንም ሕዝባችንንም ይፈጃል” አሉ።

12 ያልሞቱትን ደግሞ ዕባጩ ያሠቃያቸው ስለ ነበር፣ የከተማዪቱ ጩኸት እስከ ሰማይ ወጣ።