1 ሳሙኤል 6:8-14 NASV

8 የእግዚአብሔርን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ በታቦቱም አጠገብ ባለው ሣጥን ውስጥ ለበደል መሥዋዕት የምትልኩትን የወርቅ ምስሎች አስቀምጡ፤ በፈለገውም መንገድ እንዲሄድ ልቀቁት፤

9 ነገር ግን ወዴት እንደሚሄድ ተመልከቱ፤ ወደ ቤትሳሚስ አቅጣጫ ወደ ገዛ አገሩ የሚሄድ ከሆነ፣ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው። ወደዚያ ካልሄደ ግን፣ መከራው በአጋጣሚ የደረሰብን እንጂ የእርሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን።”

10 እነርሱም እንደዚሁ አደረጉ። ሁለቱን ላሞች ወስደው በሠረገላው ጠመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውንም በቤት ውስጥ ዘጉባቸው።

11 የእግዚአብሔርንም ታቦት፣ የወርቁን ዐይጦችና የዕባጮቹን ምስሎች በሠረገላው ላይ ጫኑ።

12 ከዚያም ላሞቹ መንገዳቸውን ይዘው እምቧ እምቧ እያሉ ቀጥ ብለው ወደ ቤትሳሚስ አመሩ። የፍልስጥኤም ገዦችም እስከ ቤትሳሚስ ድንበር ተከተሏቸው።

13 በዚህ ጊዜ የቤትሳሚስ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴአቸውን ያጭዱ ነበር፤ ቀና ብለው ሲመለከቱም ታቦቱን በማየታቸው በጣም ደስ አላቸው።

14 ሠረገላውም ወደ ቤትሳሚስ ወደ ኢያሱ ዕርሻ መጥቶ በአንድ ትልቅ ቋጥኝ አጠገብ ቆመ። ሕዝቡም የሠረገላውን ዕንጨት ፈልጠው፣ ሁለቱን ላሞች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር አቀረቡ።