1 ሳሙኤል 9:20-26 NASV

20 ከሦስት ቀን በፊት ስለ ጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ፤ ተገኝተዋልና። የእስራኤል ምኞት ሁሉ ያዘነበለው ወደ አንተና ወደ አባትህ ቤተ ሰብ ሁሉ አይደለምን?”

21 ሳኦልም፣ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ጐሣዬስ ከብንያም ነገድ ጐሣዎች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለ ምን ትነግረኛለህ?” ብሎ መለሰለት።

22 ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አመጣ፤ ከተጋበዙትም ሠላሳ ያህል ሰዎች ሁሉ በላይ አስቀመጣቸው።

23 ሳሙኤልም ወጥ ቤቱን፣ “ለይተህ አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን የሥጋ ብልት አምጣው” አለው።

24 ወጥ ቤቱም የጭኑን ሥጋ እንዳለ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም፣ “ይህ፣ ‘እንግዶችን ጋብዣለሁ’ ካልሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ስለ ሆነ ብላው” አለው። ሳኦልም በዚያች ዕለት ከሳሙኤል ጋር አብሮ በላ።

25 ከማምለኪያው ኰረብታ ወደ ከተማዪቱ ከወረዱ በኋላ ሳሙኤል በቤቱ ሰገነት ላይ ከሳኦል ጋር ተነጋገረ።

26 በማለዳ ተነሡ፤ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፣ “ላሰናብትህ ስለ ሆነ ተዘጋጅ” አለው። ሳኦልም ተዘጋጅቶ እንዳበቃ፣ ከሳሙኤል ጋር ተያይዘው ወደ ውጭ ወጡ።