1 ሳሙኤል 9:4-10 NASV

4 ስለዚህ በኰረብታማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አካባቢ ባለው ስፍራ ሁሉ ተዘዋወረ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኙም። ወደ ሻዕሊምም ግዛት ዘልቀው ገቡ፤ አህዮቹ ግን በዚያም አልነበሩም። እንዲሁም በብንያም ግዛት በኩል ዐለፈ፤ ሆኖም አላገኟቸውም።

5 ወደ ጹፍ ግዛት በደረሱ ጊዜ ሳኦል አብሮት የነበረውን አገልጋይ፣ “አባቴ ይህን ጊዜ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር፣ ና እንመለስ” አለው።

6 አገልጋዩ ግን፣ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት።

7 ሳኦልም አገልጋዩን፣ “መሄዱን እንሂድ፤ ነገር ግን ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ አልቆአል። ለእግዚአብሔር ሰው የምናበረክተውም ስጦታ የለንም፤ ታዲያ ምን አለን?” አለው።

8 አገልጋዩ፣ “እኔ የአንድ ሰቅል ጥሬ ብር ሩብ አለኝ፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ዘንድ ገንዘቡን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ” ሲል በድጋሚ መለሰለት።

9 ቀደም ሲል በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፣ “ኑ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ” ይል ነበር፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበርና።

10 ሳኦልም፣ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ።