9 ከኬብሮን ዘሮች፣አለቃውን ኤሊኤልንና ሰማንያ የሥጋ ዘመዶቹን፤
10 ከዑዝኤል ዘሮች፣አለቃውን አሚናዳብንና አንድ መቶ ዐሥራ ሁለት የሥጋ ዘመዶቹን።
11 ከዚያም ዳዊት ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፣ ሌዋውያኑን ኡርኤልን፣ ዓሣያን፣ ኢዩኤልን፣ ሸማያን፣ ኤሊኤልንና አሚናዳብን ጠርቶ፣
12 እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ እናንተ የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ስለ ሆናችሁ፣ እናንተና ወንድሞቻችሁ ሌዋውያን ራሳችሁን ቀድሱ፤ ከዚያም የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ወዳዘጋጀሁለት ቦታ አምጡ።
13 የአምላካችን የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችን ላይ እንዲህ የነደደው እናንተ ሌዋውያኑ ቀድሞም ስላላመጣችሁት ነው፤ እኛም ብንሆን ምን ማድረግ እንዳለብን በታዘዘው መሠረት አልጠየቅነውም።”
14 ስለዚህ ካህናቱና ሌዋውያኑ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት ራሳቸውን ቀደሱ።
15 ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው፣ ሌዋውያኑ የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎች አድርገው ተሸከሙ።