1 ዜና መዋዕል 18:8-14 NASV

8 ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ሰሎሞን የናሱን ባሕር፣ ዐምዶቹንና ልዩ ልዩ የናስ ዕቃዎቹን የሠራው በዚሁ ነበር።

9 የሐማት ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሰራዊት ሁሉ ድል እንደመታ ሲሰማ፣

10 እጅ እንዲነሣውና ደስታውንም እንዲገልጥለት ልጁን አዳራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቶዑ ከአድርአዛር ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት ገጥሞ ነበር። አዶራምም ከወርቅ፣ ከብርና ከናስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ዕቃዎች አመጣለት።

11 ንጉሥ ዳዊት ከኤዶም፣ ከሞዓብ፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጥኤማውያንና ከአማሌቃውያን ከእነዚህ ሁሉ መንግሥታት የማረከውን ወርቅና ብር ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሰ።

12 የጽሩያ ልጅ አቢሳ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያን ገደለ።

13 እርሱም በኤዶም የጦር ሰፈሮች አቋቋመ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።

14 ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።