1 ዜና መዋዕል 21:12-18 NASV

12 የሦስት ዓመት ራብ ወይስ የጠላቶችህ ሰይፍ ለሦስት ወር አይሎብህ መጥፋት ወይስ ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ መቅሠፍት በምድሪቱ ላይ ወርዶ የእግዚአብሔር መልአክ እስራኤልን ሁሉ ያጥፋ?’ ለላከኝ ምን እንደምመልስ ቍርጡን ንገረኝ።”

13 ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ መሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ።

14 ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መቅሠፍት ላከ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰው ዐለቀ።

15 እንዲሁም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉ መልአክ ላከ፤ መልአኩ ሊያጠፋትም ሲል እግዚአብሔር አይቶ ስለሚደርሰው ጥፋት አዘነ፤ ሕዝቡን የሚያጠፋውንም መልአክ፣ “እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

16 ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔር መልአክ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ አየ፤ መልአኩም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ እንደ ለበሱ በግምባራቸው ተደፉ።

17 ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የበደልሁት እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ።

18 ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።