1 ከዚያም ዳዊት፣ “ከእንግዲህ የእግዚአብሔር አምላክ ቤት በዚህ ይሆናል፤ እንዲሁም ስለ እስራኤል የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚሁ ይቆማል” አለ።
2 ስለዚህ ዳዊት በእስራኤል የሚኖሩ መጻተኞች እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ከመካከላቸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ጥርብ ድንጋይ እንዲያዘጋጁ ጠራቢዎችን መደበ።
3 ለቅጥር በሮቹ ምስማርና ማጠፊያ የሚሆን ብዙ ብረትና ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስ አዘጋጀ።
4 እንዲሁም ሲዶናውያንና ጢሮሳውያን በብዛት አምጥተውለት ስለ ነበር፣ ስፍር ቍጥር የሌለው የዝግባ ዕንጨት አሰናዳ።