1 የእስራኤል የቤተ ሰብ አለቆች፣ የሻለቆች፣ የመቶ አለቆች እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ በየወሩ የሚመደቡትን ዋና ዋና ክፍሎች በተመለከተ ንጉሡን ያገለገሉ አለቆቻቸው ዝርዝር ይህ ነው። እያንዳንዱ ዋና ክፍል ሃያ አራት ሺህ ሰው ነበረው።
2 በመጀመሪያው ወር የመጀመሪያው ዋና ክፍል የበላይ የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም ሲሆን፣ በሥሩ የሚታዘዙ ሃያ አራት ሺህ ሰዎች ነበሩ።
3 እርሱም የፋሬስ ዘር ሲሆን፣ በመጀመሪያው ወር የሰራዊቱ ሹማምት ሁሉ የበላይ ነበር።
4 በሁለተኛው ወር የክፍለ ጦሩ የበላይ አዛዥ አሆሃዊው ዱዲ ሲሆን፣ የዚሁ ክፍል መሪ ደግሞ ሚቅሎት ነው፤ በሥሩም ሃያ አራት ሺህ ሰው ነበረ።
5 በሦስተኛውም ወር የሦስተኛው ክፍለ ጦር የበላይ አዛዥ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ ዋናው እርሱ ሲሆን፣ በሥሩ ሃያ አራት ሺህ ሰው ነበረ።
6 ይህም ከሠላሳዎቹ ይልቅ ኀያል ሲሆን፣ የሠላሳዎቹ የበላይ ነበረ፤ ልጁ ዓሚዛ ባድም የክፍሉ ሰራዊት አዛዥ ነበረ።