4 “ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንድነግሥ ከቤተ ሰቤ ሁሉ እኔን መረጠ፤ መሪ እንዲሆንም ይሁዳን መረጠ፤ ከይሁዳም ቤት የእኔን ቤተ ሰብ መረጠ፤ ከአባቴ ልጆች መካከል ደግሞ በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ ፈቃዱ ሆነ።
5 እግዚአብሔር ብዙ ልጆች ሰጥቶኛል፤ ከወንዶቹ ልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ደግሞ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።
6 እንዲህም አለኝ፤ ‘ቤቴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ ምክንያቱም ልጄ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ።
7 አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምንጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ’።
8 “እንግዲህ አሁንም ይህቺን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሱአቸው፣ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዛችኋለሁ።
9 “አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውከው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
10 ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።