1 ዜና መዋዕል 29:10-16 NASV

10 ዳዊትም በመላው ጉባኤ ፊት እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል አመሰገነ፤“የአባታችን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአንተ ምስጋና ይሁን።

11 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይናበምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።

12 ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤አንተም የሁሉ ገዢ ነህ፤ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው።

13 አምላካችን ሆይ፤ አሁንም እናመሰግንሃለን፤ለከበረው ስምህም ውዳሴ እናቀርባለን።

14 “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ቸርነት እናድርግ ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው?

15 እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው።

16 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው።