1 ዜና መዋዕል 29:21-27 NASV

21 በማግስቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም አቀረቡ፤ ይህም አንድ ሺህ ወይፈን፣ አንድ ሺህ አውራ በግ፣ አንድ ሺህ የበግ ጠቦት ሲሆን፣ ከመጠጥ ቊርባኖቻቸውና ከሌሎች መሥዋዕቶች ጋር ስለ እስራኤል ሁሉ በብዛት አቀረቡ።

22 በዚያችም ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በታላቅ ደስታ በሉ፤ ጠጡም።ከዚያም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ዐወቁ፤ ገዥ እንዲሆንም በእግዚአብሔር ፊት ቀቡት፤ ሳዶቅንም ካህናቸው እንዲሆን ቀቡት።

23 ሰሎሞንም ነግሦ በአባቱ በዳዊት ምትክ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ተከናወነለት፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት።

24 የጦር አለቆቹና ኀያላኑ ሁሉ እንዲሁም የንጉሡ የዳዊት ወንዶች ልጆች በሙሉ ታማኝነታቸውን ለንጉሥ ሰሎሞን አረጋገጡለት።

25 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ሁሉ እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከእርሱ በፊት ለነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ያላጐናጸፋቸውን ንጉሣዊ ክብር ሁሉ ሰጠው።

26 የእሴይ ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር።

27 እርሱም በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት፣ በአጠቃላይ አርባ ዓመት ነገሠ።