1 ዜና መዋዕል 29:3-9 NASV

3 ከዚህም በቀር ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሣ ለዚህ ለተቀደሰ ቤት ከዚህ በፊት ከሰጠሁት በተጨማሪ ለዚሁ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብር እሰጣለሁ፤

4 ይህም ሦስት ሺህ መክሊት የኦፊር ወርቅና ሰባት ሺህ መክሊት ንጹሕ ብር ለቤተ መቅደሱ የግድግዳ ግንብ ማስጌጫ

5 እንዲሁም ለወርቁ ሥራ፣ ለብሩ ሥራ፣ በባለ ሙያዎች ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሆን ነው። ታዲያ ዛሬ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?”

6 ከዚያም የቤተ ሰቡ መሪዎች፣ የነገዱ የእስራኤል ሹማምት፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም በንጉሡ ሥራ ላይ የተመደቡ ሹማምት በፈቃዳቸው ሰጡ፤

7 ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሰጡትም አምስት ሺህ መክሊት ወርቅ፣ ዐሥር ሺህ ዳሪክ ወርቅ፣ ዐሥር ሺህ መክሊት ብር፣ ዐሥራ ስምንት ሺህ መክሊት ናስ አንድ መቶ ሺህ መክሊት ብረት ነው።

8 የከበሩ ድንጋዮች ያለውም ሁሉ፣ በጌድሶናዊው በይሒኤል አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አስገባ።

9 ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው።