1 ዜና መዋዕል 9:18-24 NASV

18 እርሱም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በንጉሡ በር እስካሁን ድረስ ተመድቦአል። እነዚህም የሌዋውያኑ ሰፈር በር ጠባቂዎች ነበሩ።

19 የቆሬ ልጅ የአብያሳፍ ልጅ፣ የቆሬ ልጅ ሰሎምና ከእርሱም ቤተ ሰብ የሆኑት ቆሬያውያን ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚያስገባውን በር ይጠብቁ እንደ ነበር ሁሉ፣ እነዚህም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባውን በር ይጠብቁ ነበር።

20 በቀድሞ ጊዜ የበር ጠባቂዎቹ አለቃ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።

21 ወደ መገናኛው ድንኳን የሚያስገባውን በር የሚጠብቀው ደግሞ የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ ነበረ።

22 መግቢያ በሮቹን እንዲጠብቁ የተመረጡት ባጠቃላይ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። እነርሱም በትውልድ ሐረጋቸው መሠረት በሚኖሩባቸው መንደሮች ተቈጥረው ተመዘገቡ፤ በር ጠባቂዎቹን በዚያ ቦታ ላይ የመደቡአቸው ዳዊትና ባለ ራእዩ ሳሙኤል ነበሩ።

23 የማደሪያውን ድንኳን ማለትም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠብቁትም እነርሱና ዘሮቻቸው ነበሩ።

24 በር ጠባቂዎቹም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜንና፣ በደቡብ በሚገኙት በአራቱም ማዕዘኖች ላይ ነበሩ።