1 ኢዮሣፍጥ ታላቅ ሀብትና ክብር ባገኘ ጊዜ ከአክዓብ ጋር በጋብቻ ተሳሰረ።
2 ከጥቂት ዓመታት በኋላም አክዓብን ሊጎበኝ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ብዙ በግና በሬ ዐረደ፤ ከዚያም በሬማት ዘገለዓድ ላይ አደጋ እንዲጥል አግባባው።
3 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት አብረኸኝ ትሄዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱ አብረናችሁ እንሰለፋለን” ሲል መለሰለት።
4 ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “አስቀድመህ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ” አለው።
5 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት ልሂድን ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ሂድ” ብለው መለሱለት።