1 አሜስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ አልነበረም።
3 መንግሥቱን ካጸና በኋላ፣ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ሹማምት በሞት ቀጣቸው።
4 እግዚአብሔር በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው ሕግ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም ስለ ወላጆቻቸው አይገደሉ” ብሎ ባዘዘው መሠረት አደረገ እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም።
5 አሜስያስ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰብስቦ፣ እንደየቤተ ሰቡ በሻለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል በመላው ይሁዳና በብንያም መደባቸው። ከዚያም ዕድሜያቸው ሃያና ከሃያ በላይ የሆናቸውን ሰብስቦ፣ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ ሆነው ጋሻና ጦር መያዝ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺህ ሰዎች አገኘ።
6 እንዲሁም በመቶ መክሊት ጥሬ ብር አንድ መቶ ሺህ ተዋጊዎች ከእስራኤል ቀጠረ።
7 ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤልም ሆነ ከማናቸውም የኤፍሬም ሕዝብ ጋር አይደለምና፣ እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ከአንተ ጋር አይዝመቱ።
8 ሄደህ ጦርነቱን በቈራጥነት ብትዋጋም እንኳ፣ የመርዳትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።”
9 አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “ታዲያ ለእነዚህ ለእስራኤል ወታደሮች የከፈልኩት መቶ መክሊት እንዴት ይሁን?” ሲል ጠየቀው የእግዚአብሔርም ሰው፣ “እግዚአብሔር ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።
10 ስለዚህ አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እርሱ የመጡትን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው አሰናበታቸው። እነርሱም በይሁዳ ላይ ክፉኛ ተበሳጭተው ነበርና በታላቅ ቊጣ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ተመለሱ።
11 አሜስያስም ኃይሉን በሚገባ አደራጅቶ ሰራዊቱን ወደ ጨው ሸለቆ መራ፤ በዚያም ዐሥር ሺህ የሴይር ወታደሮችን ገደለ።
12 የይሁዳ ሰራዊት ሌሎች ዐሥር ሺህ ሰዎች ማረኩ፤ ወደ አንድ ዓለት ዐናት ላይም አውጥተው ቍልቍል ለቀቁአቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ።
13 በዚያኑ ጊዜ አሜስያስ ያሰናበታቸውና በጦርነቱ እንዳይካፈሉ የከለከላቸው ወታደሮች፤ ከሰማርያ እስከ ቤትሖሮን ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ ሦስት ሺህ ሰው ገደሉ፤ እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።
14 አሜስያስም ኤዶማያውያንን ደምስሶ በተመለሰ ጊዜ፣ የሴይርን ሕዝብ አማልክት ይዞ መጣ፤ ለራሱም አማልክት አድርጎ በማቆም ሰገደላቸው፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው።
15 የእግዚአብሔርም ቊጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይንም ላከበት፤ ነቢዩም፣ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ ማዳን ያልቻሉትን የአሕዛብን አማልክት ርዳታ የጠየቅኸው ለምንድን ነው?” አለው።
16 እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመነሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው።ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንደወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።
17 የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ አማካሪዎቹን ካማከረ በኋላ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ኢዮአስ፣ “እስቲ ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል ላከበት።
18 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ ግን፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ‘ሚስት እንድትሆነው ሴት ልጅህን ለልጄ ስጠው’ ሲል ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከበት። ከዚያም የዱር አውሬ ከሊባኖስ ወጥቶ ኵርንችቱን ረገጠው።
19 ኤዶምን አሸንፌአለሁ ብለህ ራስህን በትዕቢት ክበኸዋል፤ ኮርተሃልም፤ ግን ዐርፈህ እቤትህ ተቀመጥ! በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ታመጣ ዘንድ ችግር የምትጠራው ስለምንድን ነው?”
20 የኤዶምን አማልክት ማምለክ በመፈለጋቸው፣ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኖአልና፣ አሜስያስ አላዳመጣቸውም።
21 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ አደጋ ጣለ። እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ በይሁዳ ውስጥ ቤትሳሚስ በተባለ ስፍራ ፊት ለፊት ተጋጠሙ።
22 ይሁዳ በእስራኤል ክፉኛ ተመታ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደየመኖሪያው ሸሸ።
23 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ከኤፍሬም በር እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አንድ መቶ ሰማንያ ሜትር ያህል ርዝመት ያለውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ።
24 እርሱም በዖቤድ ኤዶም ጥበቃ ሥር የነበረውንና በቤተ መቅደሱ የተገኘውን ወርቅ፣ ጥሬ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ ከቤተ መንግሥቱም ንብረትና በመያዣ ከያዛቸው ሰዎች ጭምር ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
25 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአስ ከሞተ በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
26 በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነው ሌላው ተግባር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
27 አሜስያስ እግዚአብሔርን መከተል ከተወ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ስላመፁበት ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ ነገር ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ከኋላው ልከው በዚያው በለኪሶ ገደሉት።
28 በፈረስ ተጭኖ ከመጣ በኋላም፣ እንደ አባቶቹ ሁሉ በይሁዳ ከተማ ተቀበረ።