2 ዜና መዋዕል 3 NASV

ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ሠራ

1 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ላይ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ዳዊት ባዘጋጀው ቦታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።

2 በነገሠም በአራተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በሁለተኛው ቀን ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመረ።

3 ሰሎሞን ለሕንጻው የጣለው መሠረት በቀድሞው ስፍር ልክ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር።

4 በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ላይ ያለው በረንዳ ርዝመቱ በቤተ መቅደሱ ወርድ ልክ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ከፍታውም ሃያ ክንድ ነበር። ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።

5 የቤተ መቅደሱን ዋና ክፍል በጥድ እንጨት አልብሶ በተጣራ ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳልም ቀረጸበት።

6 ቤተ መቅደሱን በከበረ ድንጋይ አስጌጠው፤ የተጠቀመበትም ወርቅ የፈርዋይም ወርቅ ነበር።

7 የጣራውን ተሸካሚዎች፣ መቃኖችን፣ የቤተ መቅደሱን ግድግዳና መዝጊያዎች በወርቅ ለበጠ፤ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቤልን ምስል ቀረጸ።

8 እንደዚሁም ቅድስተ ቅዱሳኑን ሠራ፤ ርዝመቱ ከቤተ መቅደሱ ወርድ ጋር እኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ስፋቱም ሃያ ክንድ ነበር፤ ውስጡንም በስድስት መቶ መክሊት የተጣራ ወርቅ ለበጠው።

9 የወርቅ ምስማሮቹም አምሳ ሰቅል ይመዝኑ ነበር፤ የላይኛውንም ክፍሎች እንደዚሁ በወርቅ ለበጠ።

10 በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሁለት ኪሩቤል ምስል አስቀርጾ በወርቅ ለበጣቸው።

11 ከዳር እስከ ዳር ገጥሞ የተዘረጋው የኪሩቤል ክንፍ በጠቅላላው ሃያ ክንድ ነበር፤ የመጀመሪያው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሆኖ የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ሲነካ፣ ሌላው አምስት ክንድ የሆነው ክንፉ ደግሞ የሁለተኛውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።

12 እንደዚሁም የሁለተኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሆኖ በአንጻሩ ያለውን የቤተ መቅደስ ግድግዳ ሲነካ፣ አምስት ክንድ የሆነው ሌላው ክንፉ ደግሞ የመጀመሪያውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።

13 የተዘረጋው የእነዚህ ኪሩቤል ክንፍ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ፊታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ዋና ክፍል አዙረው በእግራቸው ቆመዋል።

14 ደግሞም ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከደማቅ ቀይ ፈትልና ከቀጭን በፍታ መጋረጃ ሠርቶ፣ የኪሩቤልን ምስል በጥልፍ ጠለፈበት።

15 በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በአንድነት ቁመቱ ሠላሳ አምስት ክንድ የሆነ፣ በእያንዳንዱም ላይ አምስት ክንድ ጒልላት ያለው ሁለት ዐምድ ሠራ።

16 እርስ በርሳቸው የተጠላለፉ ሰንሰለቶች ሠርቶ ከዐምዶቹ ጫፍ ጋር አገናኛቸው፤ ከዚያም መቶ የሮማን ፍሬዎች ሠርቶ ከሰንሰለቶቹ ጋር አያያዛቸው።

17 ዐምዶቹንም አንዱን በደቡብ፣ ሌላውን በሰሜን አድርጎ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በደቡብ በኩል ያለውን፤ “ያኪን”፣ በሰሜን በኩል ያለውንም “ቦዔዝ” ብሎ ጠራቸው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36