1 ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የራሱን ቤተ መንግሥት የሠራባቸው ሃያ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣
2 ኪራም የሰጠውን ከተሞች አድሶ እስራኤላውያን እንዲሰፍሩባቸው አደረገ።
3 ከዚያም ሰሎሞን ወደ ሐማት ሱባ ዘመተ፤ ያዛትም።
4 በምድረ በዳውም ውስጥ ተድሞርንና ቀድሞ በሐማት ሠርቶአቸው የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ ሠራ።
5 እንዲሁም የላይኛውን ቤት ሖሮንና የታችኛውን ቤትሖሮን የተመሸጉ ከተሞች አድርጎ ከቅጥሮቻቸው፣ ከበሮቻቸውና ከመዝጊያዎቻቸው ጋር ሠራ።
6 ደግሞም ባዕላትንና የዕቃ ቤት ከተሞቹን ሁሉ፣ ሠረገሎችና ፈረሶች የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሁሉ፣ ባጠቃላይ በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በግዛቱ ሁሉ ለመሥራት የፈለጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሠራ።
7 እስራኤላውያን ያልሆኑ ግን ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዜያውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩት ሕዝቦች ሁሉ፣
8 እስራኤላውያን ያላጠፏቸውን፣ በምድሪቱ የቀሩ ዘሮቻቸውን የጒልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሰሎሞን መለመላቸው፤ እስከ ዛሬም ይሠራሉ።
9 ይሁን እንጂ ሰሎሞን ማንም እስራኤላዊ ባሪያ ሆኖ በግዳጅ ሥራውን እንዲሠራ አላደረገም፤ እነርሱ ተዋጊዎች፣ የሻምበል አዛዦች፣ የሠረገሎችና የሠረገላ ነጂዎች አዛዦች ነበሩና።
10 ከእነዚህም ሁለት መቶ አምሳዎቹ የንጉሥ ሰሎሞን ሹማምት ሰዎቹን የሚቈጣጠሩ ነበሩ።
11 ሰሎሞንም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ቦታ ሁሉ ቅዱስ ስለ ሆነ፣ ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤተ መንግሥት መኖር አይገባትም” በማለት የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ እርሱ ወደሠራላት ቤተ መንግሥት አመጣት።
12 ሰሎሞንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ፊት ለፊት ባሠራው የእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ።
13 ሙሴ ስለ መሥዋዕት አቀራረብ ባዘዘው መሠረት በእያንዳንዱ የበዓል ቀን ይኸውም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻና በሦስቱ የዓመት በዓላት ማለትም በቂጣ በዓል፣ በመከር በዓልና በዳስ በዓል ጊዜ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ።
14 የአባቱን የዳዊትን ሥርዐት በመከተልም፣ ካህናቱን በየአገልግሎት ክፍላቸው ሌዋውያኑንም ምስጋናውን እንዲመሩና በየዕለቱ ሥራቸው ካህናቱን እንዲረዱ መደባቸው። ደግሞም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች በልዩ ልዩ በሮች ጥበቃ ላይ በየክፍላቸው መደባቸው።
15 እነርሱም ንጉሡ ግምጃ ቤቱን ጨምሮ ስለማናቸውም ነገር ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሰጠውን ትእዛዝ አልተላለፉም ነበር።
16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ዕለት አንሥቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው የሰሎሞን ሥራ ሁሉ ተከናወነለት፤ በዚሁ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ከፍጻሜ ደረሰ።
17 ከዚያም ሰሎሞን የኤዶም የባሕር ጠረፍ ወደሆኑት ወደ ዔዮንጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ።
18 ኪራምም ባሕሩን በሚያውቁት በራሱ መኮንኖች የሚታዘዙ መርከቦችን ላከለት፤ እነዚህም ከሰሎሞን ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ኦፊር ተጓዙ፤ ከዚያም አራት መቶ አምሳ መክሊት ወርቅ አምጥተው ለንጉሥ ሰሎሞን ሰጡት።