2 ዜና መዋዕል 20:17-23 NASV

17 ይህን ጦርነት የምትዋጉት እናንተ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁንም ማዳን እዩ። አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገውኑ ውጡና ግጠሙአቸው፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል።’ ”

18 ኢዮሣፍጥ በግምባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ሰገዱም።

19 ከቀዓትና ከቆሬ ወገኖች ጥቂት ሌዋውያንም ቆመው፣ እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

20 በማግሥቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ አድምጡኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።

21 ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሠራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣“እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ።

22 መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም።

23 የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ።