6 እንዲህም አለ፤“የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በሰማይ የምትኖር አምላክ አይደለህምን? የምድር ሕዝቦችን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፤ ሊቋቋምህም የሚችል ማንም የለም።
7 አምላካችን ሆይ፤ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳድደህ ያስወጣህና ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘላለም የሰጠሃቸው አንተ አይደለህምን?
8 እነርሱም ተቀመጡባት፤ ለስምህ መቅደስ ሠሩባት፤ እንዲህም አሉ፤
9 ‘የፍርድ ሰይፍም ሆነ የቸነፈር ወይም የራብ መከራ ቢደርስብን ስምህ በተጠራበት በዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት፣ በፊትህ ቆመን በጭንቀታችን ወደ አንተ እንጮሃለን፤ አንተም ትሰማናለህ፤ ታድነናለህም።’
10 እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ግዛታቸውን እንዳይወርሩባቸው በማድረግህ ከእነርሱ ተመልሰው ሳያጠፏቸው የቀሩት የአሞን፣ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች እነሆ እዚህ አሉ።
11 እነሆ፣ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር እኛን በማፈናቀል ወሮታ ሊመልሱልን መጥተዋል።
12 አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ አቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።