1 ኢዮሣፍጥ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮሆራምም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
2 የኢዮሆራም ወንድሞች የሆኑት የኢዮሣፍጥ ልጆችም ዓዛርያስ፣ ይሒኤል፣ ዘካርያስ፣ ዔዛርያስ፣ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ይባላሉ። እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ።
3 አባታቸውም ብዙ የብርና የወርቅ፣ የውድ ዕቃዎችም ስጦታ እንዲሁም በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሰጣቸው፤ ነገር ግን መንግሥቱን ለኢዮሆራም ሰጠ፤ የበኵር ልጁ ነበርና።
4 ኢዮሆራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋር በሰይፍ ገደለ።
5 ኢዮሆራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።
6 እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።