2 ዜና መዋዕል 24:16-22 NASV

16 እርሱም በእስራኤል ውስጥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ መልካም ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ በነገሥታቱ መቃብር ተቀበረ።

17 ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ ሹማምት መጥተው ለንጉሡ ታማኝነታቸውን ገለጡ፤ ንጉሡም አዳመጣቸው።

18 እነርሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ትተው፣ የአሼራን ዐምዶችና ጣዖታትን አመለኩ፤ በበደላቸውም ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።

19 ወደ እግዚአብሔር ይመልሷቸው ዘንድ እርሱ ነቢያቱን ወደ ሕዝቡ ሰደደ፤ ነቢያቱም መሰከሩባቸው፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም።

20 የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቶአችኋል” አላቸው።

21 እነርሱ ግን አሤሩበት፤ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

22 ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ በዚህ ፈንታ ልጁን ገደለው፤ በሚሞትበትም ጊዜ፣ “እግዚአብሔር ይየው፤ እርሱው ይበቀልህ” አለ።