1 ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት።
2 አሜስያስ እንደ አባቶቹ ሁሉ ካንቀላፋ በኋላ፣ ኤላትን እንደ ገና የሠራት፣ ወደ ይሁዳም የመለሳት ዖዝያን ነበር።
3 ዖዝያን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
4 እርሱም አባቱ አሜስያስ እንደ አደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
5 እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።
6 በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጌትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ።