2 ዜና መዋዕል 28:1-7 NASV

1 አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር እንዳደረገው እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም።

2 በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በኣሊምን ለማምለክም የተቀረጹ ጣዖታትን ሠራ።

3 እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያስወገዳቸውን አሕዛብ ልማድ በመከተል፣ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ዐጠነ፤ ወንዶች ልጆቹንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።

4 በኰረብታ መስገጃዎችና በተራሮች አናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ።

5 ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም ብዙዎቹን ምርኮኞች አድርገው ወደ ደማስቆ ወሰዷቸው። ደግሞም ለእስራኤል ንጉሥ አልፎ ተሰጠ፤ እርሱም ከባድ ጒዳት አደረሰበት።

6 ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺህ ወታደሮች ገደለ።

7 ጦረኛው ኤፍሬማዊ ዝክሪም የንጉሡን ልጅ መዕሤያን፣ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን ዓዝሪቃምንና ለንጉሡ በማዕረግ ሁለተኛ ሰው የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።