2 ዜና መዋዕል 28:15-21 NASV

15 በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቁታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።

16 በዚያን ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤

17 ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና።

18 ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በየኰረብታው ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ያሉትን ከተሞች በመውረር ቤትሳሚስን፣ ኤሎንን፣ ግዴሮትን፣ ሦኮን፣ ተምናን፣ ጊምዞንና በአካባቢአቸው የሚገኙትን መንደሮች ሁሉ ያዙ፤ ተቀመጡባቸውም።

19 የእስራኤል ንጉሥ አካዝ ክፋትን በይሁዳ ምድር ስላስ ፋፋና ለእግዚአብሔርም የነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ደረጃ ስላጓደለ፣ እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደ።

20 የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም።

21 አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ጥቂት ዕቃዎች ወስዶ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶ ነበር፤ ይህም አልረዳውም።