1 ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም አቡ የተባለች፤ የዘካርያስ ልጅ ነበረች።
2 አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
3 በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ከፈተ፤ አደሳቸው።
4 ካህናቱንና ሌዋውያኑን አስገብቶ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ላይ በመሰብሰብ፣
5 እንዲህ አላቸው፤ “እናንት ሌዋውያን፤ ስሙኝ! ራሳችሁን አሁኑኑ ቀድሱ፤ የአባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀድሱ። ርኩስ ነገርንም ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ።