2 ዜና መዋዕል 29:31-36 NASV

31 ከዚያም ሕዝቅያስ፣ “እነሆ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል፤ አሁንም ቅረቡ፤ መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጉባኤው መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ አመጡ፤ ልባቸው የፈቀደ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።

32 ጉባኤውም ያመጣው የሚቃጠለው መሥዋዕት ብዛት ሰባ ወይፈኖች፣ መቶ አውራ በጎችና ሁለት መቶ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ናቸው፤ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ ነበሩ።

33 ለመሥዋዕት የተቀደሱት እንስሳት ባጠቃላይ ስድስት መቶ ወይፈን፣ ሦስት ሺህ በጎችና ፍየሎች ነበሩ።

34 ይሁን እንጂ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ሁሉ ለመግፈፍ ቊጥራቸው እጅግ ጥቂት ነበር፤ ስለዚህ ወገኖቻቸው የሆኑት ሌዋውያን ሥራው እስኪያልቅና ሌሎች ካህናት እስኪቀደሱ ድረስ ረዷቸው፤ ሌዋውያኑም ራሳቸውን ለመቀደስ ከካህናቱ ይልቅ ጠንቃቆች ነበሩና።

35 ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋር የሚቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት ስብና የመጠጡን ቍርባን ጨምሮ የሚቃጠለው መሥዋዕት እጅግ ብዙ ነበር። በዚህ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንደ ገና ተደራጀ።

36 ሕዝቅያስና ሕዝቡ ነገሩ ሁሉ እንዲህ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲከናወን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሐሴት አደረጉ።